Wednesday, August 1, 2012

“የመለስ ጤንነት ከበፊቱ እየተሻሻለ ነው”- በረከት ሰምዖን


በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጤንነት ላይ ለሚወራው ለእያንዳንዱ አሉባልታ መንግሥት ምላሽ እንደማይሰጥ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን ማስታወቃቸውንና ጤንነታቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ሪፖርተር በዛሬው እትሙ ዘግቧል፡፡
እንደ ሪፖርተር ዘገባ ካለፈው እሑድ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕይወታቸው አልፏል የሚል ወሬ በከተማው ሲናፈስ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ትናንትና የኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕን ምንጭ አድርጐ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረፋቸውን ዘግቧል፡፡
ሆኖም ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤንነት ጉዳይ ብዙ ዕውቀት እንደሌለው ገልጾ፣ ስለጤንነታቸውም ምንም ዓይነት ግምት መሰንዘር እንደማይችል በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የተላለፉት ዘገባዎችን እንደማያውቃቸው ገልጿል፡፡
በኢሳት የተላለፈው ዘገባ ለሰዓታት እንኳን ያልቆየ ውሸት ነው ያሉት አቶ በረከት፣ እንደ ምንጭነት የተጠቀመው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ዜናውን ወዲያው አውግዞታል ብለዋል፡፡ ‹‹የተለያዩ ተቃዋሚዎች ዓላማቸው ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት መናገር ሳይሆን፣ በኅብረተሰቡ ላይ ግራ መጋባትን በመፍጠር በጉዳዩ ለማትረፍ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ስትራቴጂያቸው መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱን አሉባልታ እያሳደድን ምላሽ መስጠት ጉዳዩን ያባብሰዋል እንጂ መፍትሔ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዕረፍት ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ በረከት፣ የጤንነት ሁኔታቸው ከበፊቱ እየተሻለ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የት እንዳሉና መቼ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ግን አሁንም ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መታመማቸው በይፋ የተገለጸው ባለፈው ሰሞን በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ሲሆን፣ የሕመማቸው ምክንያት ካለባቸው የሥራ ጫና ብዛት የመጣ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዘም ያለ ዕረፍት እንዲያደርጉ በሐኪሞቻቸው ተመክረዋል መባሉ ይታወሳል ሲል” ሪፖርተር ጽፏል።
የአቶ መለስ ዜናዊ በህይወት የመኖር አለመኖር ወይም ወደ ሥራቸው ለመመለስ በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ስለመሆናቸው በዘገባው የተገለጸ የለም። ሥራ ስለበዛባቸው እረፍት ላይ ናቸው፣ የሐኪም እረፍት ላይ ናቸው፣ የሉም ሞተዋል፣ አሉ ግን ኮማ ውስጥ ናቸው፣ አዲስ አበባ ገብተዋል ሰሞኑን መግለጫ ይሰጣሉ የሚወሉ የተለያዩ ዘገባዎችና አስተያየቶች በየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው።

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)