Friday, November 18, 2011

ብርቱካን በአንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ የተናገሩ

ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ፓሪስ በተደረገ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ስብሰባ ላይ ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል። ብርቱካን የተናገሩት በመንግሥታቱ ድርጅት ሕገ ወጥ እስርን አስመልክቶ የሚሰራው አካል (United Nations Working Group on Arbitrary Detention) 20ኛው ዓመት በዓል ላይ ነው።
ወ/ት ብርቱካን፣ በዓለም አቀፋዊው መድረክ የተጋበዙት፣ የሕገ ወጥ እስር ሰለባ የነበሩ በመሆናቸውና፣ በዚያም ሳቢያ ያሳለፉትን አስከፊ የስቃይ ዓመታት ለመማሪያነቱ እንዲያወጉ ነው። እንዲሁም ድርጅቱ ጉዳያቸውን ከተከታተለላቸው የዓለም እስረኞች አንዷ ናቸው። ስለሆነም የድርጅቱን አወንታዊ ሥራ እንዲመሰክሩ፣ ብሎም በአገራቸውም ሆነ በሌሎች በርካታ አገሮች የሕገ ወጥ እስር ሰለባ ስለሆኑ ሰዎች መፍትሔ እንዲያመላክቱ ነው።
የህግ ባለሙያዋ ብርቱካን ለዘኢትዮጵያ ጋዜጣ እንደገለጹት “በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ፣ እንደ አንድ አካል ሆኖ፣ ህገወጥ እስርን አስመልክቶ የሚሰራው ይህ የድርጅት የሚከታተለው፣ የስምምነቱ ፈራሚ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚከሰት ህገ ወጥ እስር ሲኖር ነው። ህገወጥ በሆነ መንገድ ሰው በሚታሰርበት ወቅት፣ ማንም ሰው ጉዳዩን ለድርጅቱ አካል ማመልከት ይችላል። ጉዳዩም በማንኛውም ሰው አቤቱታ አቅራቢነት የሚታይ ጉዳይ ሆኖ፣ አቤቱታው በዓለም አቀፋዊ ህግና መርህ አንጻር ተገቢነቱ ይመረመራል። ተገቢው ማጣራትና የህግ ምርምር ከተደረገ በኋላ፣ ድርጅቱ የራሱን የመጨረሻ የህግ ውሳኔ ሀሳብ የመስጠት ሥልጣን አለው። በዚህ መሠረት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ጫና በማሳደር በርካቶችን ከእስር ያስለቀቀ አካል ነው።
የድርጅቱ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ወ/ት ብርቱካንም በታሰሩ ጊዜ የታሰሩበት ጉዳይ፣ ህገ ወጥና ዓለም አቀፍ የሰብአዊመብቶችን (the Universal Declaration of Human Rights articles 9, 10, 19, 20 and 21) ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን  (the International Covenant on Civil and Political Rights articles 9, 14, 19, 21, 22 and 25) የጣሰ መሆኑን ዘርዝሮ በመግለጽ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፉን በእለቱ ይፋ ካደረገው ዳታና ከአንዱ የውሳኔ ሰነድ ብቻ ማየት ይቻላል።
የመንግሥታቱ ድርጅት፣ እንደ አንድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት፣ ውሳኔ የሚሰጠው፣ የህግ አግባቦችን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና የተፈጸሙ ጥሰቶችን ከመረመረ በኋላ ነው። ይህን ጥሰው የተገኙ አገሮችንም ጠርቶ የሚያነጋግር ሲሆን፣ የኢትዮጵያም መንግስት በወቅቱ ምላሽ ሰጥቶበታል።
በዘንድሮው የድርጅቱ ስብሰባም ላይ ተገኝተው፣ ንግግር እንዲያደርጉ ከተመረጡት እውቅ የዓለም እስረኞች መካከል፣ በሶሪያው የቀድሞ ዳኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኼይተም አል ማለህ፣ ኢትዮጵያዊቷ ወ/ር ብርቱካን፣ እና የኖቤል ተሸላሚዋ ሎሬትና የዲሞክራሲ አክቲቪስት፣ የበርማዋ ኡኝ ሳን ሱ ኪ ናቸው። ሳን ሱ ኪ መልእክታቸውን በቪዲዮ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሌሎቹ ሁለቱ በአካል በመገኘት ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ በዚያ መድረክ በመናገር ብርቱካን የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።
ወ/ሮ ብርቱካን በልዩ  ጨለማ ቤት፣ ለረጅም ጊዜ መሰቃየቱ እንዳለ ሆኖ፣ በህግ ደግሞ አቤት ማለትም ሆነ ምንም ውሳኔ ማግኘት አለመቻል ተደራቢ ጥቃት ነው ብለዋል። ይህን ነገር ፍርድ ቤት አቀርባለሁ፣ አቤት እላለሁ... ማለት አለመቻልን የመሰለ አስከፊ ነገር የለም። “...ይህን ነገር ፍ/ቤት አቀርባለሁ ምናምን ብትይ...” እየተባለ የሰው ልጅ  ፍትህ ሳያገኝ የሚኖርበት አገር የሚያሳድረው ስሜት ልዩ መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል። 
ግፍና ጭቆና የዘወትር ተግባር በሆነበት አገር ተስፋ ማድረግ አስቸጋሪ ነገር ነው። ይህን ሁሉ ነገር አሸንፎ ሊወጣ በሚችል የሰው ልጅ አቅም ግን ጠንካራ እምነት አለኝ። ይህ ትውልድ ያለመቻቻልና ያለመግባባትን ፖለቲካ ሊለውጥ እንደሚችል አምናለሁ። በመንግሥትና በዜጎች መካከል ያለውንም ግንኙነት መልክ ማስያዝ ይቻላል የሚል ተስፋ አለኝ። እስር ቤት ሁለተኛ ቤታቸው እስኪመስላቸው ድረስ የራሱን ዜጎች የሚያሰቃይና የሚያሸብር መንግሥት የሌለባት አገር መፍጠር ይቻላል።” ብለዋል።
“ከኛ መስማት የፈለጉት ውሳኔያቸው ምን ያህል ጥቅም እንደሰጠንና ነጻነት ማጣት ሊያደርስ የሚችለውን ነው። ልምዴ የጨለማ ቤቱ ፍዳ (ቶርቸር) እንዴት ከባድ እንደሆነ መናገር ነው። ሀሳቤን በመግለጼ ምን እንደ ደረሰብኝ፣ የደረሰብኝን ግፍ ምስክርነት መስጠት ነው። “ከጨለማው ቤት ተዘግቶ ለብቻ መታሰር፣ ዓላማው ውጫዊውን አካል ብቻ ሳይሆን ፣ውስጥን ሰባብሮ ለማድቀቅ ነው። ያ ግፍ ምን ቃል ይገኝለታል?” ።
 “ይሄ አካል ከዓለም አቀፍ ህግና የሰብአዊ መብት መርህ አንጻር የደረሰብኝን አይቶ ይህን መወሰኑ፣ ለኔ ነጻነት ያስገኘው ጥቅም ከፍተኝ ነው ብዬ ነው የማምነው “ ብለዋል።
“የሚገርመው ነገር” ብለዋል ወ/ሮ ብርቱካን “ባለፉት 40 ዓመታት ይደርስ የነበረው ግፍ ስለባ የነበሩ ሰዎች ሳይቀሩ ዛሬ ገብተውበታል። ለምሳሌ አጎቴ ማእከላዊ ሆኖ በቀይሽብር እንደተሰቃየ አስታውሳለሁ። ዛሬ እሱና ጓደኞቹ ደግሞ በተራቸው ባለሥልጣን ሆነው እነ እስክንድርን ያሰቃያሉ ። ይሄ ድግግሞሽ - መቆም አለበት። ይህን ሊለውጥ የሚያስችል በቂ አቅም ግን አለን ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ሰው የሚጎዳ መንግሥት ነው ያለን” ማለታቸውን አጫውተውናል።
የፈረንሳይ የድርጅቱ መስራች በመሆንዋ ኖርዌይ ደግሞ የዘንድሮውን ዝግጅት በማሳነዳት የረዳች በመሆንዋ ባንዲራቸው በተባበሩት መንግሥታት ሰንደቅ ግራና ቀኝ ሆኖ ከመድረኩ ጀርባ ይታያል። የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ባለሥልጣናትና የጀርመንና የመሳሰሉት መንግሥታት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተወካዮችም ተገኝተዋል። የብዙ አገር መንግሥታት ተወካዮቻቸውን ልከዋል።
“አንዲትም ነገር አልተናገሩም እንጂ ከኢትዮጵያም የመጡ ተወካዮች ነበሩ።”

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)