Tuesday, April 26, 2011

ያለፈው ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት እየታሰሩ ነው

42 የመድረክ አባላትና ደጋፊዎች ታሰሩ
ሃይለሥላሴ ተስፋይ
በ 2010 ምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩና የመድረክ ኣባል ከሆኑት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄና የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ 42 ኣባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸው ተነገረ። ተቃዋሚዎቹ የታሰሩት ከምዕራብ ሸዋ፣ ከምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ተወስደው መሆኑንም ተገልጿል። በመቀሌ ያለው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይመስልም።
ለምሳሌ የአረና ትግራይ አባል የሆነው ተክላይ አርአያ በትግራይ የደረሰበትን ነገር ሁሉ መቻል አቅቶት ወደ አዲስ አበባ መሰደድ ተገዶ ነበር። አዲስ አበባም ገብቶ ግን እስሩ አልቀረለትም። ቢሆንም እዚህ ሲታሰር ቢያንስ የውሸትም ክስ ቢሆን ይመሰረትበታል። እናም “የቀድሞ የትግራይ ፓርላማ አፈ ጉባኤ አቶ ወልደ ሩፋኤል አለማዮሁን በስልክና ፅሁፍ ተሳድባሃል” ተብሎ
ተከሰሰ። ለክሱም ዳኛ ሳይጠበቅ ታሰረ። አሁን ሦሰት ሳምንት ሆኖታል። ማንም ሰው እንዳይጠይቀው ተከልክሏል። ተክላይ በዚሁ የሐሰት ውንጀላ ከሦሰት ዓመት በፊት መቀሌ ላይ ታስሮ ተፈቷል። የአሁኑ እስር ትክክለኛ ምክንያት ግን በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳው የህዝብ ማዕበል ይመስላል። ምክንያቱም አቶ መለስ ዜናዊና ህወሓት በዚህ ተደናግጠዋል። የፈሩትንና የጠረጠሩትንም ሁሉ አስቀድመው የሚያስሩት ለዚህ ነው ብለው የሚናገሩ አሉ። ያም ሆነ ይህ ግን ከአካባቢው ከሚደርሱን ዘገባዎች መረዳት እንደምንችለው አፈናው ማስፈራራቱና ክትትሉ ቀጥሏል።
በተለይ በወጣቱና በተቀዋሚ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ላይ ዛቻና ማሰፈራሪያዎች እየጨመሩ መጥተዋል።ሁኔታው አቶ መለስ ዜናዊ ባለፈው ፓርላማ ላይ ከሰጡት አጠቃላይ ማስጠንቀቂያና ዛቻ ጋር የተያያዘ ይመስላል። ምክንያቱም ባለፈው ምርጫ የተወዳደሩት እነማን ናቸው? ህዝቡን ሲያስተባብሩ የነበሩትስ የትኞቹ ናቸው? አሁን የትን ነው ያሉት? ምን እያደረጉ ነው? የመሳሰሉት ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። አርፈው ተቀመጡም አልተቀመጡም
ባለፈው ያደረጉት ፋይል ሁሉ ይወጣል። ይህ አመጽ ለሚያስቡት ሁሉ ማስፈራሪያ ይመስላል። የመድረክ ድርጅት አባል በሆኑ ግለሰቦችና ደጋፊዎቻቸው ላይ ግን ዛቻ ሳይሆን እስር፣ ወከባና ድብደባ በቀጥታ እየደረሰ ነው።
ለምሳሌ መድረክን ወክለው፣ በትግራይ፣ በውቅሮ፣ ማረይ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ አያሌው በየነ ከቤታቸው ከተኙበት በሌሊት ተቀስቅሰው ተወስደዋል። ቤተሰቦቹና የአካባቢ ሰዎች እንደገለጹልን አቶ አያሌውን በላንድክሉዘር መኪና ወስደው እስኪበቃቸው ድረስ ከደበደቡ በኋላ አሰቃይተው ከቤታቸው 50 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ጥለዋቸው ሄደዋል። ሽሬ እንዳስላሴ ላይ ጥዋት እንደ እቃ ተጥለው የተገኙት አቶ አያሌው ይህን ለማንም ትንፍሽ እንዳይሉ ተንግሯቸዋል። ያን ካደረጉ የሚቀጥለው ሞት መሆኑን እንዲያውቁት የተዛተባቸው መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ አቶ አያሌው በምርጫው ግርግር ጊዜም መኖሪያ ቤታቸው ላይ ፈንጅ ተውርወሮ ቤታቸው ውስጥ መፈንዳቱን በተለያዩ የዜና አውታሮች በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአረና አመራር አካል እንደገለጹልን ህውሓት ትግራይ ውስጥ ባሉ ሌሎች የአረና ኣባላት ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው። “በአባሎቻችን የግል ህይወት ሳይቀር እየገባ ትዳራቸውን እስከማፍረስ ከቤተሰብ እስከማለያየት ወርዶ እየሠራ ነው።”የሚሉት የአመራር አካል ሚስቶቻቸውን በማስጠንቀቅና አንዳንዶቹም እንዲፈቷቸው ጣልቃ ገብቶ እስከማስገደድ የደረሰበት ሁኔታ አለ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ አራት የሚደርሱ የአረና አባላት ከባለቤቶቻቸው ጋር እንዲለያዩ መገደዳቸውን የአመራር አካሉ ገልጸዋል ።
ህወሃት አባላቱን ከማስፈራራትም ጎን ለጎን አረና የተባለውን ድርጅት ለመከፋፈልና ብሎም ለማፍረስ የራሱ ተለጣፊ እየፈጠረ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል ከፓርቲው የተባረሩና፣ የፓርቲው አበላት ያልነበሩትን አሰባስቦ አስገፈላጊው ገንዘብ በመስጠት ማደራጀት ይዟል። በመገናኛ ብዙሓንም የአረና ድርጅት መሆናቸውን በመግለጽ ሽፋን እንዲያገኙ እያደረገ ነው። እስካሁን በምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጣቸው ቢሆንም በዚሁ አያያዝ ከቀጠለ በሌሎቹ ድርጅቶች ላይ እንደታየው ቀጣዮ እርምጃ እሱ ሊሆን ይችላል።
ሌላው መንግሥት ለዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ማስፋፊያ ከውጭ አገሮች ከሚሰጠው ገንዘብ ውስጥ ለፖለቲካ ድርጅቶች የተወሰነውን የማከፋፈል ግዴታ ያለበት ቢሆንም ስድስት ፓርቲዎች ባንድላይ ለሚገኙበት መድረክ የሰጠው 3ሺ980 ብቻ መሆኑ ተገልጿል። ሁኔታው ፌዝና ተራ ቀልድ መሆኑን ከመግለጽ ጋር መድረክ አልቀበልም ብሎ መመለሱን ምንጮቻችን ገልጸውልናል።
ይህ ሆኖ ግን ህዝቡ ተቃውሞውን በድፍረት እየገለጸ መምጣቱንና ከተቃዋሚ ድርጅቶችም ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎቱን እየገለጸ መሆኑ ተመልክቷል። ለዚህ አብነት ሆኖ የተጠቀሰው መድረክ ባለፈው ሁለት ሳምነት በመቐሌ ከህዝብ ጋር ለመወያየት የጠራው ስብሰባ ነው። መድረክ ያን ስብሰባ ለመጥራት ድምፅ ማጉያ እንዳይጠቀም ተከልክሏል። ለክለካው የተሰጠው ምክንያት በምርጫ ጊዜ ካልሆነ አሁን ድምፅ ማጉያ መጠቀም አትችሉም የሚል ነበር። ይሁን እንጂ የመድረክ አባላት ያዘጋጁትን ስብሰባ ህዝቡ በራሱ የተለያዩ ዘዴዎች ሰምቶ መምጣቱ ተነግሯል። ስለወቅታዊ ሁኔታ መወያየቱና የህወሓት ካድሬዎች ግን ህዝቡ መስማት እንደማይፈልግ በመግለጽ ተቃውሞ በማሰማት ለመረበሽ መሞከራቸው
ተነግሯል። ተሰብሳቢው ህዝብ ግን መስማት የሚፈልግ መሆኑን በመግለጽ ካድሬዎቹ ራሳቸው እንዲወጡ ማድረጉና አንወጣም ያሉትንም ተገደው እነዲሰሙ በማድረግ ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ምንጮቹ ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)