Friday, February 18, 2011

Today's Headline

ምን ዓይነት ሊባኖስ ነው?
ኢትዮጵያውያንም እንደ አውሮፕላኑ በቤይሩት ሁሌም እንደተከስከሱ ነው

አሁን  በዚሁ ወር ፌብርዋሪ  2010 በሊባኖስ ቤይሩት ው ስጥ  እንኳ አንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣት ከአራተኛ ፎቅ ራሷን ወርውራ ገድላለች፣ የሚል ዜና ወጥቷል። ልክ እንደሷ ከፎቅ ዘለው የወደቁ፣ ራሳቸውን ካንጠለጠሉበት ገመድ እየተጎተቱ የተጣሉ፣ በስለት የተወጉ፣ በድንጋይ የተወገሩ፣ የቤይሩት አፈር የበላቸው ጥቂት አይደሉም። ይህም በዛ ተብሎ  ሰሞኑን ከተከሰከሰው  የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር “የእናንተ አውሮፕላን ተከስክሶ የኛን ሰዎች ጨረሰብን” በሚል በቤይሩት ያሉት ኢትዮጵያዊያን ፍዳቸውን እያዩ ነው።- (ገጽ 3 ን ይመልከቱ)

ሰኞ ጃንዋሪ 25/2010 ማለዳው ላይ ልክ ከቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ እንደተነሳ በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የነበሩ 90 መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞች በሙሉ አልቀዋል። ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ 51 የሊባኖስ ዜጎችና 23 የኢትዮጵያውያን መንገደኞች ነበሩ።
በዚህኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ አደጋው በደረሰ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሌላኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዴግሞ ቤይሩት አውሮፕላን ጣቢያ እያረፈ ነበር። በዚያች አስቸጋሪ ጊዜ እንኳ በረራው አልተቋረጠም። ምክንያቱም አየር መንገዳችንን ወደ ሊባኖሷ ቤይሩት የሚያመላልሰው ብዙ ጉዳይ አለው። በጣም ብዙ ነገር።
ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ “ቤይሩት 50ሺ ኢትዮጵያዊያን አሉ” ብለዋል። ለአንዲት ከተማ 50ሺ ብዙ ነው።
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ሚያዚያ 22/2000 የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜ አንድ መግለጫ አውጥቶ ነበር። “ወደ ቤይሩት የሚደረገውን ማንኛውም የስራ ስምሪት ከሚያዝያ 16 ጀምሮ በመንግስት የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ቤይሩት እንዳይልክ” በማለት አስጠንቅቋል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ዴኤታ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ የሥራ ስምሪቱ የተቋረጠው በሊባኖስ ቤይሩት የሚደረግ የሥራ ስምሪት ለዜጎች ደህንነት አስጊ እየሆነ በመምጣቱ ነው። በሊባኖስ ቤይሩት ለስራ በሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ምግብ መከልከል፣ ቤት በላያቸው ላይ መዝጋት፣ ጾታዊ ጥቃትና የመሳሰሉት በደሎች እንደሚደርሱባቸው ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ ፤ በሚደርስባቸው የስራ ጫና፣ በደል፣ የባህልና ቋንቋ ተጽዕኖ የተነሳ ለሞት የሚዳረጉም እንዳሉ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ህጋዊ ፈቅድ ያላቸው ኤጀንሲዎች ሳይቀሩ የተለያዩ ቪዛዎችን በመጠቀም ዜጎችን ወደ ቤይሩት ከመላክ  አልተቆጠቡም። በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ቤይሩት በመሄድ በስራ ላይ የተሰማሩ ከ50 ሺ የሚበልጡ ዜጎች መኖራቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑን የሚልካቸው ማነው?
ግማሹ መንግሥት ራሱ ነው ሲል ከፊሉ ደግሞ ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው ይላል። ጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ ታውቆ የሚፈጸምና ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ሳይቀር በተደረገ ስምምነት የሚካሄድ መሆኑን ግን በግልጽ የሚያስረዱ ዘገባዎች አሉ። ለምሳሌ “የኢትዮጵያ እና የሊባኖስ መንግስታት ፌብሩዋሪ 1/2006 የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ወደቤይሩት (ሊባኖስ) ለመላክ መስማማታቸውን” በወቅቱ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። በዘገባው መሠረት 8 ሺህ ወንዶች እና 30 ሺህ ሴቶች ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ወደ ቤይሩት የሚላኩ ሲሆን ይኽን ለማስፈፀም ስምንት ያህል ኤጀንቶች ተቋቁመው እያንዳንዳቸው በቤይሩት 37ሺ ዶላር ፤ በኢትዮጵያ 25 ሺ ዶላር ዲፖዚት አስቀምጠው ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያንን ሴቶች ብዙዎች ወደሚንገላቱባት ቤይሩት የመላኩ ድርጊት የሚፈጸመው በሁለቱ መንግሥታት ስምምነትና እውቀት ነው። ፈቃድ አውጥተው ገንዘብ ተቀብለው የሚልኩ ድርጅቶች ቢኖሩም የ“ኤክስፖርት” ማበረታቸውን የሚሰጠው መንግሥት ነው። ንግዱን የሚያጧጡፉት ከመንግሥት የተለዩ ግለሰቦች ተደርገው ከተቆጠሩ ማለት ነው።

አውሮፕላናችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንም  በቤይሩት ሁሌም እንደተከስከሱ ነው!
“እንዴ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? እኛስ ሰዎች አይደለንም? የሞቱት ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን አይደሉም እኛ እስከዚህ ድረስ ምን አደረግን?”
ይህ በአደጋው የሞቱባቸውን ቤተሰቦች ሁኔታ ለማጣራት ሮጠው ቤይሩት ኤርፖርት ከደረሱት ኢትዮጵያውያን አንዷ በወቅቱ ለውጭ ጋዜጠኞች የተናገረችው ነው። በአደጋው ተደናግጠው በኤርፖርቱ የተገኙ ኢትዮጵያውያኑ ተነጥለው ለብቻቸው አንድ ክፍል ታጉረው እንዲቆዩ በመደረጋቸው ተበሳጭታ ነው ። እንደሷ እንጀራ ፍለጋ የመጣችው የአጎቷ ልጅ  ወደ ኢትዮጵያ በመብረር ላይ እያለች አየር ላይ ቀርታለች። እሷ ደግሞ በሌሎች ፊት በተናቀው ዜግነቷ ወደዚያ ተገፍትራ በወጉ እንኳ ማልቀስ አልቻለችም። በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን  መሳቅ ብቻ ሳይሆን ማልቀስም ክልክል ይሆን እንዴ?
ሲባል እንደተኖረው ሊባኖስ በተለይ ለሴቶቻችን አይመችም። በአውሮፕላኑ አደጋ ከሞቱት ኢትዮጵያውያን መካከል እንኳ አንዷ ገና ከእስር ቤት ተለቃ ወደ አገሯ ማቅናቷ ነበር። የእህቶች ሰቆቃ ብዙ ነው።
ከፎቅ ዘለው የወደቁ፣ ራሳቸውን ካንጠለጠሉበት ገመድ እየተጎተቱ የተጣሉ፣ በስለት የተወጉ፣ በድንጋይ የተወገሩ፣ የቤይሩት አፈር የበላቸው ጥቂት አይደሉም። ግራ አጋቢው ነገር ግን ሊባኖስም ሆነ ወደሌሎቹ አረብ አገሮች መሰደድ እድለኞች ብቻ የሚታደሉትና ብዙ ዋጋ ከፍለው የሚያገኙት “ሎተሪ” እየሆነ ነው። ያለቀው አልቆ የተረፈው እንዲኖር የተፈረደ ይመስላል። ይህም በዛ ተብሎ “የእናንተ አውሮፕላን ተከስክሶ የኛን ሰዎች ጨረሰብን” በሚል በቤይሩት ያሉት ኢትዮጵያዊያን ፍዳቸውን እያዩ ነው። በኤርፖርቱም የደረሰባቸው ይኸው ነው።  “ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች” እየተባሉ በየቦታው መጠራታቸው አንሶ፣ ሌላው ግፍና በደላቸው ሁሉ ተረስቶ፣ እህቶቻቸው ሳይቀር ባለቁበት አደጋ ተጠያቂ እየሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ነገር ለማስቆም የተደረገ ነገር ባይኖርም ዜናው ግን ሁሌም እንደተነገረ ነው። በቤይሩት ሳላሉ ኢትዮጵያውያን በግልና በመንግሥት ጋዜጦች ሳይቀር በተለያየ ዓመት የወጡ ርዕሰ ዜናዎች ብዙዎች ከመሆናቸው የተነሳ ፋይል አገላብጦ ለመልቀም እንኳ አላስቸገሩም። ዘኢትዮጵያ ካሰባሰባቸው ርእሰዜናዎች እነዚህ ጥቂቶቹ  ይገኙበታል-

ወጣቷ ቤይሩት ውስጥ ታረደች
•    (ከጎሕ ግንቦት 21 ቀን 1991)
•    ቤይሩት ከሄደች ወር ያልሞላት ወጣት አስክሬኗ ተመለሰ
•    (ከገናናው ኅዳር 16 ቀን 1992)
•    በቤይሩት የኢትዮጵያዊቷ አስክሬን የደረሰበት ጠፋ
•    (ከአዲስ አድማስ ሚያዝያ 28 ቀን 1992)
•    ኢትዮጵያውያኑ በሊባኖስ መደብደባቸውን ድርጅቱ አስታወቀ
•    (ከአዲስ ዘመን የካቲት 23 ቀን 1993)
•    በሊባኖስ የ25 ሺህ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ችግር ተባብሷል
•    (ከኔሽን ጥቅምት 16 ቀን 1995)
•    80 ኢትዮጵያውያን ሴቶች በቤይሩት እስር ቤት ውስጥ ያለጠያቂ ናቸው፤
•    ግንቦት 7 ድምጽ ኖቨምበር 2009
•    በቤይሩት ለእንግልት ተዳርገው የነበሩ 34 ኢትዮጵያውያን ተመለሱ.
•    21 ጁላይ 2009 ...የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

እና ምን ይሆን የሚጠበቀው?

1 comment:

 1. Your blog is great你的部落格真好!!
  If you like, come back and visit mine: http://b2322858.blogspot.com/

  Thank you!!Wang Han Pin(王翰彬)
  From Taichung,Taiwan (台灣)
  WELCOME

  ReplyDelete

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)