Friday, February 6, 2009

በሚሊኒየሙ ለፍቅር እንበድ!

2000 ዓመተ ምህረት ሊሆን ነው። ሚሊኒየም መባሉ 19 መቶውን ሸኝተን 2000ውን ልንቀበል በመቃረባችን ነው። የምንቀበለው አዲስ ዓመት አይደለም። አዲስ ምእተ (መቶ) አመት ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ይህን የሽግግር ጊዜ በህይወት ያለው ሁሉ እኩል ይቀበለዋል። አገር ቤት ያለው፣ ስደት ያለው፣ ቤተመንግሥት ያለው፣ እስር ቤት ያለው፣ ዲታውም ቺስታውም ሁሉም እኩል ይቀበለዋል። ሁሉም በያለበት ሆኖ ይሸጋገረዋል። ልዩነቱን ልዩ ብሎ ላሰበ ይሆንለታል። ያው ዝምብሎ ቁጥር ነው ለሚለውም ቁጥር ይሆንበታል። ቢሆንም ለሁለቱም ዘመን በቁጥር መለወጡ የግድ ነው። ተወደደም ተጠላም፣ ተመቸም ተቸገረም ዘመን መለወጡ አይቀርም። ቁምነገሩ ከዘመኑ ጋር እንዴት ያለ ለውጥ ይኑረን የሚለው ነው።

ህይወት ጣዕሟ፣ ካሉበት የተሻለ ህይወት ማጎናጸፏ ነውና፣ የተሻለ ህይወት ቢኖረን፣ ሁላችንም እንመኛለን። ከአዲሱ ምእተ ዓመትም የምንጠብቀው ይህንን ነው። ለራሳችንም፣ ለልጆቻችንም ለህዝብና ለአገራችንም፣ ይህን በፍቅር ብንመኝ ነውርነት የለውም። ምኞታችን እንዴት ይሁን ነው ጥያቄው! ምኞት መልክ ሲይዝ ጥሩ ነው። ምኞት ከጥሩ ህሊናና ልብ ሲመነጭ ደስ ያሰኛል። ወይም ግትርና እቡይ ልብን አሸንፎ ለንሰሃ ሲዘጋጅ፣ ለብሩህ ተስፋ ሲሰናዳ፣ አዲሱ ምዕተ ዓመት ለኢትዮጵያችን ጥሩ ይሆናል። እነንሳ!

አዲስ ይሁን ሲባል አዲስ ይሁን። እርቅ ሲባል እርቅ ይሁንልን። ያለፈውን ሁሉ እንርሳ ሲባል የሆነ ሆኗል ከማለት ብቻ ሳይሆን የሆነው ተመልሶ እንዳይሆን ከማሰብ ጭምር ነውና ልባችን ወከክ ብሎ ይከፈት። እንሸነፍ። ነገሮች እንዴት እንደማይቻሉ ሳይሆን ነገሮች እንዴት እንደሚቻሉ የምናስብበት ጥበብ የምናገኝበት ዘመን ይሁንልን። ጨለማውን ዘመን ለመተንበይ ጠቢብ አያስፈልገንም። ምክንያቱም ጨለማ በጥበብ አይመጣም። ብርሃን ግን ከጥበበኛ ይገኛል። ብርሃን እንይ። ይህ ስካር ከሆነ ወይም ቅዠትም ከመሰለ ይምሰል። ጨለማን ከመቃዠት ብርሃንን መቃዠት ይሻላል። ጎበዝ 100 ዓመት ለእንዲህ ያለ ምኞት ብዙ ነው።

እስረኞች ይፈቱ። ሰደተኞች ወደአገራቸው ይግቡ። የተፈረደባቸው ምህረት ይውረድላቸው። የመንግሥት ባለሥልጣናት ነገ ተመልሰው ከሥልጣን ቢወርዱ ምንም የማያገኛቸው ሰለመሆኑ ዘለዓለማዊ ዋስትና ይሰጣቸው። ከቅዠት ሁሉ ይኸኛው ቅዠት ደስ ይላል።

የሸዋ ልጆች ትግራይን ሄደው ያልሙ። የትግራይ ልጆች ወለጋ ይሂዱ። ወለጎች ጎንደርን ያበልጽጓት። ባሌዎች ጎጃም ይሂዱ። ጎጃሞች ሲዳሞ ይውረዱ። ጋሞጎፋ ሶማሌ ጉራጌም አፋር ወሎም አርሲ ይሂዱ ሁሉም ይደበላለቅ። ለሰርጋችን መልስ ለመልሱ ቅልቅል እንጥራ። ከፈለጋችሁ ሚሊኒየሙን እንዲህ አድርገን እናክበረው።

ለአቶ መለስ ዜናዊ ለኢኒጂነር ኃይሉ ሻውል ሐውልት ይቁምላቸው። ለአቶ ልደቱ መንገድ ይሰየምላቸው። ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ፕሬዚዳንት ይሁኑ። ኢህአፓዎች የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ካቢኔ ያቋቁሙ። ፕሮፌሰር መስፍን ወይም ራስ መንገሻ ስዩም ወይም ሌንጮ ለታ ወይም ኦባንግ ንጉሥ ይሁኑ። ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ስለተሰራው ስህተት እየዞሩ ታሪክ እንዳይደገም ያስተምሩ። አገራቸው መጦሪያ ትሁናቸው። በስህተት ላለቁት ወጣቶች ሁሉ ትውልድ ሙዚየም ይስራላቸው። ቤተሰቦቻቸው በየሄዱበት ክብርን ያግኙ። ኤርትራውያን ደስ እሳካላቸው ድረስ በነጻነት እንዲኖሩ ኢትዮጵያ ትርዳቸው። ወንድም ጎጆ ሲወጣ መርዳት ምን አለበት። ህጻናት አንተ ጋላ አንተ ወሎዬ አንተ አጋሜ አንተ ጎንደሬ አንተ ጎጃሜ አንተ መንዜ አንተ ጉራጌ እየተባባሉ ይቀላለዱ። ማንነት ህመም አይሁናቸው። ሲያድጉ ተጋብተው እንዲዋለዱ ተዋልደው እንዲዋሃዱ ሁሉም የገዛው ጎሳውን የገዛ አካባቢውን ለፍቅር ሲል አሳላፎ ይስጥ። አብሮ የመኖር ጥበብ ወደ ኢትዮጵያ ትመለስ!

ኢትዮጵያ በሙስሊሞቿም ትታወቅ። ኢትዮጵያም ነቢዩ እንዳሏት፣ ቅዱስ ቁርአን እንደጻፋት ትሁን። የስደቱ ሲኖዶስና የአገር ቤቱ ሲኖዶስ አንድ ይሁኑ። አባቶች የፍቅር አባት ይሁኑ። ቅዱስ አባታችን አቡነ ጳውሎስና ቅዱስ አባታችን አቡነ መርቆሪዮስ ከመንበር ፓትሪያርኩ በረንዳ ላይ አብረው ተቀምጠው "ወይ ጉድ! እኛ አባቶችንኮ ሰይጣን አስቶን ነበር ብለው " እየተሳሳቁ ስለድሮው ስላሳለፉት የጸብ ዘመን ይጫወቱ። "እርሶ ይቅደሙ! የለም እርስዎ ይቅደሙ!" እየተባባሉ በክብር ይግደርደሩ። ኢትዮጵያ ይህን አይታ ትሙት!

አል አሙዲ ያሰሩት በአፍሪካ ትልቁ ዩኒቨርስቲ ወይም ትልቁ ሆስፒታል፣ ሲመረቅ ህዝብ ቆሞ ሳያቋርጥ ያጨብጭብላቸው። እሳቸውም "እናንተ ግን በጣም ትገርማላችሁ የዛሬ ስንት ዓመት ህይወቴን ለዚያ መንግሥት እሰጣለሁ ስላልኩ ሌባ ሌባ ትሉኝ ነበር ዛሬ ግን አዳሜ ቆመሽ አጨበጨብሽልኝ ብለው ይቀልዱ።" ህዝቡም ፍርስ ብሎ ይሳቅ። በምርቃቱ ላይ አሜሪካን አገር ቡሽን ኪሊንተንን ካርተርን ሪፐብሊካን ዴሞክራትን አንድ ላይ ቆመው እንደምናያቸው የግርማነታቸውን የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን ልጅ ልጆች በሙሉ ጨምሮ፣ኮ/ል መንግሥቱን ኃ/ማርያምን፣ አቶ መለስን፣ዶ/ር ነጋሶን፣ ፕሬዚዳንት ግርማን ፍቅረ ሥላሴ ወ/ግደረሰን፣ ታምራት ላይኔን፣ ፕሮፌሰር መስፍንን፣ ኃይሉ ሻውልን፣ዳውድ ኢብሳን፣ ብረሃኑ ነጋን፣ በረከት ሰምዖንን፣ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ስዩምን መስፍንን፣ አቦይ ስብሀትን፣ መርሻ ዮሴፍን፣ ስዬ አብርሃን፣ ፋሲካ በለጠን፣ ጎሹ ወልዴን፣ ኢያሱ ዓለማየሁን ፣ ገላሳ ዲልቦን፣ አረጋዊ በርሄን፣ ሌንጮን፣ በየነን፣ መረራን፣ ቡልቻን፣ ልደቱን፣ አርከበን፣ ሌሎችንም ሁሉ ወደፊት ከሚመጡትና በምርጫ ካሸነፉት መሪዎች ጋር ተደርድረው እንያቸው።

ዓለም ጉድ ይበል። ኢትዮጵያ በፍቅር ትሰከር። ጠላትህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚለው እንደመፈክር መስቀል ወይም አብዮት አደባባይ ላይ በትልቁ ይጻፍ። እርቅ የምንሰብክበት ሳይሆን የምንታረቅበት ይሁንልን። መጪው ሚሊኒየም ይህ የሚሳካበት ቢሆን ምን አለበት? መቸም በለው፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው ማለትም ያው ስካር ነው። ለስካር ለስካር ደግሞ ይኸኛው ይመቻል። ካበዱ ላይቀር ምናለበት! (ዘኢትዮጵያ)

1 comment:

  1. Although I didn't really understand Amharic.But anyway,welcome to my blog.
    http://b2322858.blogspot.com/

    ReplyDelete

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)