Friday, February 6, 2009

ኧረ ስለ እግዜአብሄር!

ማሽላን ከወፍ እንዲጠብቅ የተቀጠረ እረኛ ወፍ ማባረሪያ ጠጠር የሚያቀብለው ሌላ እረኛ ቀጠረ ይባላል። ራስን አጓጉል ከፍ ከፍ የማድረግና ያልተገባ ሥልጣንን የመፈለግ አባዜ ከጥንት ከጧቱ የነበረ መሆኑን የሚያመላክቱ እንዲህ ዓይነት አባባሎችን አባቶች አቆይተውልናል። እንግዲህ እረኛም ምክትል እረኛ ከቀጠረ እረኝነቱን በአንድ የሥልጣን ደረጃ ከፍ የማድረግ አሳብ አለው ማለት ነው። ምክትሉ እረኛም፣ የእረኛም ምክትል አለው- ብሎ ሲያስብ፣ አንድ ቀን "መፈንቅለ እረኛ" አካሂዶ ዋነኝነቱን እረኝነት እንደሚረከብ ተስፋ ማድረጉ አይቀርም።

ህዝብ እንዲያገለግሉ በህዝብ የተመረጡት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ድጋፍ ሰጪዎች መለመሉ። ወይም ድጋፍ ሰጪዎቹ እኛ ጠጠር እናቀብላችኋለን ብለው አመለከቱና የድጋፍ ሰጪነቱን ሥፍራ ተረከቡ። በመካከልም ክፉ አጋጣሚ ሆነና መሪዎቹ ታሰሩ። እስረኞችም ተረሱ። ድጋፍ ሰጪዎቹ ወዲያው ራሳቸውን በአልጋ ወራሽነት አስሾሙና ምክትል ድጋፍ ሰጪዎችን የዓለም አቀፍ ፣ የስሜን አሜሪካ፣ ዲሲ የቨርጂኒያ የካሊፎርኒያ የምንትስ ቻፕተር ቻርተር እያሉ ሾሙ። ከዚያ በኋላ ምን ቀረ? ምንም። በኢትዮጵያ ጉዳይ እስከመወያየት በቁና አንዳንድ ብሔራዊ ጉዳዮችንም እስከመወሰን ደረሱ። ውሳኔያቸውንኳ ሳይጽፉት ግን ተጣልተው ተባሉ። ገንዘብ ያገኙ ገንዘቡን ነገር የተረፋቸው ነገሩን በሉ ተባለ። ቅንጅት ሊደግፉ የተነሱት እንደጌታ ቀሚስ ስሙን ቀዳደው ተከፋፈሉት። አንድ ሰው ብቻውን ቅንጅት ነኝ የሚልበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም። አቤት ትዕቢት!

በኢትዮጵያ ጉዳያ አንድ ሰው ከተሰጠው ወይም ራሱን ከአጨበት የአገልጋይነት ቦታ ተነስቶ በአንድ ሌሊት አብጦ የሚገኝበት ምክንያት ህዝባዊ ኃላፊነትን የቁልቁለት መንገድ አስመስሎታል። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሰው የማልችለው የማልመጥነው የኃላፊነት ቦታ የለም ብሎ ማሰቡ በራሱ የሚያስገርም እየሆነ ነው። መንግሥት በሚኒስትርነት ወይም በሥራ አስኪያጅነት ከሚሾመው ሰው ሁሉ፣ አንድም ቀን ትህትና ኖሮት፣ "ይህንስ ቦታ እኔ አልመጥንምና ይቅርብኝ" ሲል የተሰማ አንድም ስው የለም። የእርሻ ሚኒስትር የነበረው የፍትህ ሚኒስትር ሁኖ ይዛወራል። ነገ ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ቢያደርጉት እምቢ አይልም። ያው ሰው የማእድንና የኢንድስትሪ ሆኖ ከተዛወረም ይህ እንኳ ይቸግረኛል አይልም። አልችልም ይህ የኔ ሙያ አይደለም የሚል ስው እየጠፋ ነው። አርቲስቱ ከሁለት የፖለቲካ ዘፈን በኋላ የፖለቲካ መሪ ሆኖ ያድራል። ጋዜጠኝነትማ ማንም ዘው የሚልበት የጋለሞታ ቤት መስሏል። ጋዜጠኛውም ሁለገብነት ስለሚሰማው የትኛውንም አብዮታዊ አመራር ለመስጠት ወይም እንደ ዘመቻ መኮንን በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ በዚያ ተሰለፉ የማለት ልበ ሙሉነት አለው። ለሁሉም የብቃት ማረጋጋጫው ሰርቲፊኬት "አገር ወዳድነት" ብቻ ነው። ከህዝብ መካከል ግን ይህን መርምሮ የሚጠይቅ ቢኖርም በተከታይነት አምኖ የሚያጨበጭበው መንጋ ጎልቶ ይታያል ።

ሌላም አይነት እብጠት በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በኮሚቴም ደረጃ ይታያል። ከሁለት ትናንሽ ስብሰባዎች በኋላ "የሶማሊያና የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዴት አድርገን መፍታት አለብን?" የሚል መመሪያ ለማውጣት የሚሰየም "ቆፍጣና" ኮሚቴ ማየት የተለመደ ነው። አስር መጽሐፍትን በእርዳታ ለመላክ የተሰባሰበ አንድ ኮሚቴ፣ ከሁለት ስብሰባ በኋላ "ኢትዮጵያን ከድህነት እንዴት ማላቀቅ እንችላለን?" ብሎ የውሳኔና ሀሳብና አመራር አመንጭቶ ሊያድር ይችላል። አቅምን ማወቅ ችግርንም ካማወቅ የሚመጣ ነው። "የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ምን ማድረግ አለብን?" ብሎ የሚነጋገር አንድ ኮሚቴ ገና ከመነሻው ችግር ያለበት ነው። ችግሩን ሳያዉቁ ምን ማድረግ አለብን የሚል ጥያቄ ማምጣት ፣ "ማንኛውንም መፍትሄው ለማመንጨት እንችላለን" ከሚል እብሪት የሚመነጭ ነው። በጣም በሚያሳዝን መልኩ፣ ማንኛውም ሰው የኢትዮጵያን ችግር ለማስወገድ ምን ማድረግ ይገባል ተብሎ ድንገት ቢጠየቅ "እኔ የኢትዮጵያን ችግር የማየው…" በሚል ልበ ሙሉነት ለመመለስ አፉን ሲከፍት ለሰከንድ እንኳ ሳያስብ ነው። ሁሉ ነገራችን ማን ከማን ያንሳል የሚል እየመሰለ ነው። በዚህ ቢቆም ጥሩ ነበር። እኔ እሻላላሁ እኔ በልጣለሁና እኔ የምላችሁን ብቻ ስሙኝ የሚል እብሪት እየበዛ ነው። ሲሆን ሲሆን ታዛቢ አይንና ጆሮ መኖሩን አውቆ ትንሽ አይንን ሰበር ማድረግ በተገባ ጥሩ ነበር ግን አልሆነም።

መንግሥት ሆኖ ራሱን ያነገሠብንም ድርጅትና ግለሰብ እጁ ላይ በወደቀ ሥልጣን አብጧል። የተቃዋሚዎች ድክመት ጥንካሬው ሆኖታል። የሊቃውንት ስግደት ሁሉን አዋቂ አድርጎታል። ስግብግብና ገንዘብ አምላኪ ትውልድ ወንጀለኛውን መንግሥት የሞራል ዳኛ አድርጎታል። የሚናቁት ተነጣፊዎች በዙና መንግሥት ናቂ ሆነ። አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ችግር ሚጢጢ ሆነችባቸውና "አፍሪካን ከድህነት ስለማላቀቅ" መጽሐፍ ጻፉ። ሚኒስትሮችን ናዝሬት አጎሩና በቪዲዮ ኮንፈረስ ያስተምሩ ገቡ። የመለስን ጭንቅላት በኢትዮጵያ ችግር ብቻ መለካት መለስን መናቅ ሆነ። ስለባድመ መጨነቅና ስለ ኢትዮ ኤርትራ ችግር መፍትሄ ማፈላለግ ለመለስ ዜናዊ የቀበሌ ችግር ያህል ሆኖ ቀሎ ታያቸው። ስለዚህ ትልቁን የዓለም ችግር ለመፍታት እስልምናና ክርስትናን መረጡ -ስለዚህ ጅሃድን አሸባሪ (ቴረሪስቶችን) መዋጋት መረጡ። ስለዚህ የመለስ ጭንቅላት ለዓለም ሁሉ ይበቃ ዘንድ ሥራቸውን ከሶማሌ ጀመሩ። ኤርትራ የዓለም አቀፉን ቀጠና ጥሳ 11 ታንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ስታስጠጋ እሱን ተውት እዚህ ግባ የማይሉት ትንኮሳ ነው (ማይነር ፕሮቮኬሽን ነው) አሉ። የሶማሌዎች ጅሃድ ግን ትልቅ ነውና አሜሪካም ኢትዮጵያም የአፍሪካም አገሮች ሁሉም ወደ ሶማልያ ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር ብለው አወጁ። ሰለዚህ የኢትዮጵያ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ሶማልያ ነው አልን። የሚያንገበግበንን ነገር እንኳ እያንገበገቡ የሚነግሩን ሊቁና በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የተቃጠሉት አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው። አቤት በንቀት ሲናገሩ በቴሌቪዥን ባያችዋቸው- ከእሳቸው አብዮታዊ አመራር ጋር ወደፊት!

ለማናኛውም ግን ግድ የለም እሳቸው የተመቻቸው አምባገነን መሪ ናቸውና ሁሉ ያውቃሉ እንበል፣ እኛ ግን ምንድነን? ማውራት ማውራት ማውራት ድምድም- ጥቅልል- ድፍን አድርጎ በእርገጠኝነት አስረግጦ መናገር እያበዛን ነው። የማንችለው የማናውቀው ያላስተዋልነው ብዙ ነገር አለና አንዳንዴ ረጋ እንበል። ትህትናም ጥሩ ነው። ባለቤት ባጣች፣ በደኸየች አገር ጥንቡን በጣለ መድረክ መብት ነው ብሎ ዝምብሎ መለፍለፍ ለደፋሮች ይቻል ይሆናል። ያመጣውና የሚያመጣው ምንም ነገር ግን የለም። የመናገር መብት የንግግርን እንጂ የእውቀትን መጠን አያሳይምና ልናናገረው የቻልነው ነገር ሁሉ እውነት እየመሰለን እንዳንጠፋ እግዜር ልቦናውን ይስጠን።ኧረ ስለ እግዚአብሔር እስኪ አፋችሁን ለሰከንድ ያዝ አድርጉልን እስክንባል መጠበቅ የለብንም! (ዘኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)