Tuesday, February 3, 2009

የትንሽ ሰው አጀንዳ ትንሽ ነው

ከህግ እስካልተጣላ ድረስ፣ ማንም ያሻውን ሊል፣ የሚችልበት አግባብ ይኖረዋል። ይህ ብዙዎች የሞቱለት አገራችንም የምምትጓጓለት መብት ነው። በዚህ መደራደር አይቻልም። መደራደር የሚቻለው በምርጫችን ነው። ሰው መናገር የሚችለውን አድማጭም መስማት የሚፈልገውን ይመርጣል። ችግር የሚመጣው ተናጋሪም መናገር የማይችለውን የቀባጠረ፣ አድማጭም መስማት የማይፈልገውን ለመስማት "የተገደደ" እንደሆነ ነው። ማንም ሳያስገድደው የሚያሳምመውን ሁሉ እያሳደደ የሚሰማ ካለ ግን ጉዳዩ የህግ ሳይሆን የህክምና ወይም የጠበል ይሆናል። አንዳንዶች በርግጥ ታመናል።

ተራ የመንደር ባለዝናዎችን እየተከተልን በዚህ ወጡ በዚህ ገቡ ይህን አሉ ይህን ቀባጠሩ ብለን ነገር ስናዳንቅ እንውላለን። ትንሾችና አሉባልታ ወዳጆች የሆን ይመስል ጆሯችን ሁሌም አሉባልታን ይናፍቃል። ስለ ዕውቀታችን ደረጃ ምስክሩ ጆሯችን የሚናፍቀው የውይይት ዓይነት ነው። ስድብና ንቀት ብሎም አገራዊ ውርድት ልክ እንደ ድራግና ሲጋራ ሱስ ሆኖብን ቅዳሜና እሁድ እሱን ካልጠጣን የማንውል እልፍ ነን። የሱስን ጉዳት ሱሰኛው ያውቀዋል። ግን ሊተወው አይቻለውም። ስድብና ንቀትን፣ የደናቁርትን የእብሪት ንግግርና የሎሌዎችን የተጠና ዲስኩር ሳንሰማ መዋል የማንችል ክቡራትና ክቡራን ሱሰስኞች ብዙ ነን። ጆሮውን ለስል ምላስ አጋድሞ የሰጠ ሁሉ ለምን እንደሚናደድ አይገባንም! "ምርጫ" የሚባል ነገር አለ።

ምን ያህል እንዳነስን፣ ወይም ቀድሞውንም ምን ያህል ትንሽ እንደነበርን ለማወቅ የምንሰማውን ሰው፣ የምንወያይበትን ሰውና አጀንዳ ትንሽነት ማየት ይበቃናል። ጠላት ባይኖረን ጥሩ ነው፣ ግን ለውይይት የሚበቁትን "ጠላቶቻችንን" ብናይ ምን ያህል ልናፍር በተገባን ነበር። ሲሆን ሲሆን ልናዝንላቸው፣ ካልሆነም ንቀን ልንተዋቸው የሚገቡንን ወንድሞቻችንን፣ እንደ ተፈላሚ ጠላቶቻችን አጀግነን፣ ስማቸው ካፋችን የማይጠፉ ስዎች አሉ። በአንድ በኩል እንደማይረቡ እንመስክራለን። ከዚያም አልፈን ትራሽ ውስጥ የጣልነው ቆሻሻ ነገር ነው ብለን አናንቀን እንናገራለን። ግን ከጣልንበት ትራሽ ውስጥ አውጥተን እናሸታቸዋለን። አንጨክንም። ያለነሱ አይሆንልን ይሆን?!

"ታዲያ ምን ይደረግ ሌላ አማራጭ የለንም?" ስንልም እንሰማለን። ይህ ደግሞ ሌላው አሳፋሪ ድከመት ነው። አማራጭ ማጣት አማራጭ መፍጠር ካለመቻል ድክመት የሚመጣ ነው። ትራሽ ውስጥ ከጣልነው የተሻለ አማራጭ መፍጠር ስላልቻልን፣ "ክህደቱ" ብለን ትራሽ ውስጥ የጣልነውን የወያኔ ፓርላማ ካድሬ መልሶ ማኘክ ግን መፍትሔ አይደለም። ወያኔ የሚለውን መስማት ነውርነት የለውም። ወያኔን የግድ መስማት ካለብን ግን ልንሰማቸው የሚገባንን የወያኔ ሰዎች መምረጥ አለብን። ተላላኪ ቀላጤዎቹ ሳይሆኑ፣ ዋነኞቹ እንዲያወሩን እንፍቀድ፣ እሱ እንዲያውም ትልቁ የዴሞክራሲ መሠረት ይሆነናል!

በኛ ጆሮ ህልውና ያገኙ፣ በኛ ሐሜትና የስልክ ውዳሴ አናታችን ላይ ፊጢጢ ብለው በድፍረት የሚዘባርቁ፣ ከዋነኞቹ የአገራችን አምባገነኖች በላይ ጊዜያችንን ወስደውብናል። ምርጫው ተረሳ። የሞቱት የታስሩት ቀሩ። ተረሱ። ያልተነኩትና ምላሳቸውን የተማመኑ ብልጦች አረሳስተው ተመለሱ። ትናንት በዚህ ጋዜጣ ሳያቀር " ህዝብ ከእንግዲህ ያልመረጠው መንግሥት እንዲያስተዳድረው አይፈቅምድ" ያሉትን እንዳልጻፍን እንዳልጠቅስናቸው፣ እኛ ብንረሳ ወረቀት ይረሳ መስሏቸው - ማጭበርበሪያ መልስ አጥንተው መጡ። "ብለን ነበር ወያኔኮ ይገድላል፣ ያስራል፣ ይህ መንገድ አያዋጣም" - በማለት ተናግረን ነበር አሉ። የታሰሩት ያንን የማያውቁ፣ አውቀውም በድፍረት ያላዳረጉት ይመስል፣ የገዛ ፍርሃታቸውን፣ ምናልባትም ተልዕኮና ዓላማቸውን፣ ሆድና አድርባይነታቸውን፣ ጥበብና ትንቢት አድርገው ተራቀቁብን። እና እኛም- እነዚያ ከታሰሩ መቸም ምን ይደረጋል… ብለን ፊታችንን ወደነሱ ልናዞር ተነሳን። እነዚያ ተከታዮቻቸውን አምነው - እስር ቤት እንጂ ፓርላማ አትግቡ - ተብለው የተመከሩት አባቶች፣ በጥይት የወደቁ ወንድም እህቶች ተረሱ። የከዱን ሊያስክዱን እኛም የተከዱትን አብረን ልንከዳቸው መንገድ የያዝን ይመስላል።

የታሰሩት ልክ ላይሆኑ ይችላሉ። የተገደሉትም በየዋህነታቸው ሊሆን ይችላል። ስለታሰሩ ስለተገደሉ አገርን የመምራት ሰርትፊኬት ብቃት ይሰጣቸው ማለትም አይደለም። አገር ለመምራት መመዘኛው ብቃት ነው። መስዋእትነትማ ቢሆን ስንቱ በመራ ነበር። ግን ሰዎቹ ምንም ይሁኑ ምን የታሰሩበት መንገድ ልክ ነው ልክ አይደለም? ህጋዊ ነው አይደለም? ሟቾች የተገደሉት በፍርድ ነው ወይንስ አይደለም ? የሚሉት ጥያቄዎች መሰረታዊ ናቸው። እነዚህ የቅንጅት አባላትና ደጋፊዎች ጥያቄ ብቻ ተደርገው መታሰብ የለባቸውም። እነ አቶ "ክህደቱ" ክህደት ፈጸሙ ሲባልም ይህን የተመረጡበትን የሞራል የሰብአዊ መብትና መሰረታዊ የፖለቲካና ህዝባዊ ጥያቄዎች ካዱ ማለት ነው። አርባ ጊዜ የሚታተጠፍ ቃላቸውን፣ አብረው የተማማሉ ጓዶቻቸውን መካድ፣ ምናልባትም በኛ አገር ፖለቲከኞች ዘንድ፣ የተለመደ የፖለቲካ ጥበብ ሆኖ ሊሆን ይችላል። ይሁን! ይህኛው ክህደት ግን የአቋም የመብት የንግግር ነጻነት ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ክህደት ለሰዎች መብት ብቻ ሳይሆን ባህርይም ነው። ባህርይን ደግሞ ያዉቁታል መብትነቱንም "ተፈጥሮው" ነው ብለው ከዚያው አንጻር ያከብሩታል እንጂ ቁምነገር አድርገው አይታገሉትም።

ስለዚህ እነሱን እንደሌሉ ቆጥረን ከፈጣሪዎቻቸውና ከችግሮቻችን ጋር ብንታገል ለውጥን ከምንጩ ለማምጣት ይረዳን ይሆናል። የመሰብሰብ ነጻነት የለም። የፕሬስ ነጻነት የለም። ስዎች አለፍርድ ታስረዋል፣ ተገድለዋል። "ፓርላማ ግቡ ወይ እንደ ኦነግ አገር ጥላችሁ ውጡ!" የሚል አምባገነን በአገሪቱ ነግሧል። ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በምርጫ ይመጣል ማለት አስፈርቷል። የአድፋጭ ዝምታ - ሰላም መስሏል። ኢትዮጵያ ከላይ ከታች ተከባለች። ልመና ድህነትና የኑሮ ውድነት ሞልቷል። ይህ ሁሉ ካስጠላችሁ የአዲስ አበባን አዳዲስ ህንጻዎች እያያችሁ ተጽናኑባቸው ማለት ግን ፌዝ ነው። ከሰው አልባ ድንጋይ፣ አገርና ስው ይበልጣል! (ዘኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)