Thursday, February 5, 2009

ህዝቡም አሜን ማለት አለበት!

እውርን ምን ይቫላል? ቢሉት "ማየት" አለ ይባላል። ማየት ነው።

መስማትም ይቻላል። በተለይ "አለበት" የሚል ቃል አለ። ህዝቡ አንድ መሆን "አለበት"፣ ተቃዋሚው ጠንካራ መሆን "አለበት"። ሚዲያው ነጻና ገለልተኛ መሆን "አለበት"። መንግሥትም እንዲህ ማድረግ "አለበት።" አለበት አለበት አለበት…ነው። "አለብኝ" ማለት አያስፈልግም። ብዙ ሰው ፖለቲካ ሰለማይወድ ወይም የራሱን መስዋእትነት ከፍሎ ስለጨረሰ ቀጭን መመሪያ ማስተላለፍ ይችላል። እኔ ሳልሆን ህዝቡ መታገል "አለበት"።

ኢህአፓም ኦነግም ወያኔም ሻእቢያም ደርግም ቅንጅትም ሁሉም ለሚያምኑበት መስዋእትነት ከፍለዋል። የተረፉት ተሰደዋል። በንጉሡ ዘመን የሸሸው፣ በደርግ የጎረፈው፣ በኢህአዴግ የፈለሰው ህዝብ ስፍር ቁጥር የለውም። ስደት አሁንም አለ። በዚሁ ከቀጠለ ነገም ይኖራል። በዚያች አገር የሞተው፣ የታሰረው የተሰደደው ብሎም የተቆነጠጠው ሳይቀር በዛና ሁሉም እዳውን ከፍሎ ጨረሰ። ያልወጣነው ዳገት የለምና… እናውቃለን፣ ሰለሆነም እንመራለን ማለት መጣ። ስለዚህ ሁሉም መሪ ሆነና ፣ አንዳንዱም ከፊት ከፊት ሮጥ አለና፣ ህዝቡ ተከትሎኝ መታገል "አለበት!" ይላል። አንዳንድ ጊዜ ለአገሩ ማን እንደታገለና እንዳልታገለ የሚለይ፣ እጅ ላይ የሚታሰር ምልክት ቢኖር ጥሩ ነበር። ወይም መታወቂያ ነገር ቢታደል- ይሄ "አለበት" የሚባለው "ህዝብ" ይገኝ ነበር።

መስዋእትነት የታጋይነትን ልክ እንጂ አገር የመምራት ወይም የእውቀትና ብቃትን ልክ አያሳይም። ቢሆንማ "የጀግኖች ፓርላማ" የሚባል በኖረ ነበር። መስዋእትነት በራሱ የሚደነቅ ቢሆንም ዘላቂና ትክክለኛ ዓለማን አመልካች ነው ማለትም አይደለም። የትላንት ሞት ለዛሬው ላይጠቅም ይችላል። በዚያ ላይ ዛሬ ሌላ ቀን ነው። ሟቾችም የሞቱለትን ዓላማ ይክዱታል። ሥልጣን እስኪያዝ ለዓላማ ሲባል መግደልና መሞት ይኖር ይሆናል። ሥልጣን ሲያዝ ግን ዓላማ ወዲያው ይሞታል። ታሪክ ያሳየን ይህንን ነው። እስከዚያው ግን ሁሉም ነጻ አውጪ ነው። ነጻነቱን አላየንም እንጂ ኤርትራም ትግራይም ነጻ አውጪ ኖሯቸው አይተናል። ኦነግም ያንኑ ካልደግምኩ ይላል።

በእርግጥ በየጊዜው የተከፈለው መስዋእትነት ይከበራል። ግን የትኛው መስዋእትነት ይልቃል? የማን ሞት ከማን ይበልጣል? የማንስ ስደት ይጣፍጣል? ዋናው ነገር ሞቱ ሳይሆን የተሞተበት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ወያኔዎች ለምን ሥልጣን አይለቁም? ሲባል፣ "እንዴ ለማን ብለው? ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለው እዚህ ከደረሱ በኋላ ለምን ብለው ይለቃሉ?" ይባላል። "ኢህአፓዎች ለምን አይተውትም በቃ ያ ዘመን አልፏል! - ሲባል ፣ "እንዴት? ያ ሁሉ ትውልድ አልቆ፣ የቀሩትም ሌላ ህይወት ሳያምራቸው፣ እሰከዛሬ ታግለው ሲያበቁ፣ በቃ ጥፉ ማለት አይቻልም" ይባላል። "ቅንጅቶችስ?" ሲባል "እነሱማ ይህን ያህል ተንገላተው፣ ስንት ህዝብ ሞቶ፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው እንዴት ይቀራሉ?" ይባላል። ገና እዳችንን ያላወራረዱትን ኦነጎችንም "እስኪ እንስማቸው ምናለበት… እየተባለ ነው፣ ያቺ አገር በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም፣ በጠቀማትም ባልጠቀማትም ነገር ለሞተውና ለታሰረው "ይገባኛል!" ባይ ሁሉ እዳዋን እንኳ መክፈል አልቻለችም። መስዋእትነት የሚከበር ነገር ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው፣ እንዴት መሞት፣ እንዴት መሰደድ እንደሚገባቸው እንጂ፣ በአገራቸውና ለአገራቸው እንዴት መኖር እንደሚገባቸው፣ የተገኘ አርአያነት የለም። የስንቱን ዜጋ ነፍስ ውሃ በላው። በከንቱ!

ሁሉም በየቤቱ ሙሾ አለው። ኦነግ ናቸው እየተባሉ የብዙ ኦሮሞዎች ደም በየቦታው ፈሷል። የብላቴናዎቹ ኢህአፓዎች አጽም ከመቃብር ይጮኻል። የሰሜን ተራሮችን ያጠበው የትግራይ ልጆች ደም አይረሳም። ገደል የተወረወሩ አማሮች ነፍስ እንደገደል ማሚቶ ያስተጋባል። ቅንጅትን ደገፍኩ ባለች፣ ግንባሯን በጥይት ተበቅርሳ የተደፋች ወጣት አስክሬን ገና አልደረቀም። የጋምቤላ ልጆች "የኛም ደም ቀይ ነው!" ይላሉ። ወላይታዎች ይቺ የእናንተ ሞት ብዙ ስለተጮኸላት ነው? ብለው ይታዘቡናል። የሶማሌዎች ሞት ወቅታዊ ሞት ወይም ፋሽን ስለሆነ አያስደንቅም የተባለ ይመስል አዛኝ ጠፍቷል። እስሩም ያው ነው። ኢህአፓው የማነ ገ/አብ፣ ደርጉ ፍቅረሥላሴ፣ ወያኔው ስየ አብርሃ፣ ቅንጅቱ ፕሮፌሰር መስፍን ሁሉም እስር ቤት ናቸው። ነገ ደግሞ መለስ ዜናዊ ይገባሉ። ማን ያውቃል?

ነገሮች በህዝብ አናት ይገለባበጣሉ። ለምሳሌ ኦነግ ከወያኔ፣ ኦነግ ከሻእቢያ፣ ኦነግ ከቅንጅት ጋር ቯልስ ደንሷል። ኦነግን ያወገዘ ጎበዝ፣ ለኦነግ ያጨበጨበበት ቀን ታይቷል። "ኤርትራዊ" የሚባል ቃል እንዳልሰማ ያለው ተቃዋሚ፣ "እነሱ ይሻሉናል" ሲል ተሰምቷል። ምክንያቱም ፖለቲካችን እንደዚህ ነው። "ወያኔና ሻዕቢያ" ሲል የኖረው ተቀዋሚ - "ተቃዋሚዎችና ሻእቢያ" ለመባል በቅቷል። ስዬ የኛ ነው መለስን የሻእቢያ ወኪል ነው ያሉት ወያኔዎች፣ ወዲያው ተገልብጠው ስዬን ጥለው፣ "መለስ የኛ ልጅ ነው!" ሲሉ አይተናል። በምርጫ ካርዳቸው ቅንጅትን፣ በአስላለፋቸው ወያኔን ሲመርጡም ተመልክተናል። አፋቅሮናል ያልነው ቅንጅት መልሶ ደግሞ አብራችሁ ቡና አትጠጡ ብሎናል። ቅንጅት ለቅንጅት እየተጣሉ ወያኔ ነህ - ወያኔስ አንተ ነህ ሲባባሉ እያየን ነው። ሥጋ ነው ያልነው ተበትኖ መንፈስ ሆኗል። ምክንያቱም ፖለቲካ ነው። ግራ የገባ ነገር!

ኢትዮጵያውያን ግን እንዲህ ዘመን ቶሎ ቶሎ ለሚሽረው ተራ ፖለቲካ ባንሞት ጥሩ ነበር።
የሞትንለት ነገር ራሱ ወዲያው የሚሞት ከሆነ ምንኛ ከስረናል። ለሚያልፍ ቀን ተላልፈን አንለፍ! ከዘመን ጋር እያበድን፣ ካልደፈረሰ አይጠራም እያልን ፣ ጳጳሳት የውግዘት መግለጫ የሚወነጫጨፉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። እንደተመኘነውም ደፍርሷልና አሁን ፊታችንን ወደ ማጥራቱ እናዙረው። መንግሥት ለምንለው ያለንን ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ለአፍታ ተወት አድርገን አይናችንን ብንከፍት ኢትዮጵያ የተቧደኑ ዘራፊ ጥቅመኞች እንጂ መንግሥት የላትም። እንኳን ለኢትዮጵያ፣ ለሚሸነግሉት ጎሳቸው እንኳ አይሆኑም። ስለዚህ የሌለ መንግሥት ለመጣል ከመታገል በፊት የወደፊታችንን መንግሥት የመመስረት ሥርዓትና ጥበብ እንዲኖረን ብንመኝ ሸክማችን በቀለለ፣ ብረሃንንም በተመለከትን ነበር። ካልሆነ እንጸልይ! እንኳን ለዓለማውያኑ ፖለቲከኞች ፣ ለሃይማኖት መሪዎቻችን፣ "ጌታ ሆይ አባቶቻችንም የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!" ብሎ የሚጸልይ ጠንካራ ልብም ይስጠን! ህዝቡም አሜን ማለት "አለበት!" (ዘኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)