Thursday, February 5, 2009

ያን ያህል እንኳ አልሞትንም!

አንድ ምሽት ላይ ሚስት ተደብድቦና ተፈነካክቶ የመጣ ባሏን ቁስል ትጠራርጋለች። አፍንጫው፣ ከንፈሮቹ፣ ጉንጮቹ... ቆስለዋል። ወጣ ስትል ደግሞ አይኑ አጠገብ ከቅንድቡ ሥርም ቆስሏል። በዚህ ጊዜ ደንገጥ ብላ "ውይ አንተየዋ አይንህን አጥፍተውት ነበር እግዜር ለትንሽ ነው ያወጣህ" ትለዋለች። ተደብድቦ ሚስቱ ፊት የመጣው ባል በስጨት ይልና "ዝምበይ! ምን ትላለች ይቺ... ዐይኔን እስኪያጠፉት ድረስ ሞቼያለሁ እንዴ!..." አላት ይባላል።

አንዳንዴ እኛም እንዲሁ እንሆን እንዴ? ቅንጅታችን፣ ህብረታችን፣ ኢህአዴጋችን ፣ኢህአፓችን፣ ኃይሏችን ብርሃኗችን ልደቷችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ምርጫችን፣ ቤተክርስቲያናችን፣ ዳርድንበራችን አንድነታችን፣ ተስፋችን እረ ስንቱ ነገራችን...

...ለማንኛውም ግን አገራችን ደህና ናት። ያን ያህል እንኳ አልሞትንም።

እንዲያውም በያቅጣጫው ብዙ ድሎችን እያስመዘግብን ነው። ኃይሉ ሻውል የቅንጅት እንቅፋትና ህገወጥ ያሏቸውን ሰዎች በማባራራቸው ቅንጅት ተጠናክሮ ለበለጠ ትግል የመዘጋጀቱን የምስራች እያበሰሩን ነው። እነ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የቅንጅት ህገ ደንብ ከሚያዘው ውጭ ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመዋል ያሏቸውን እነ ሊቀመንበር ኃይሉ ሻውልን በህገወጥነት ከሰው በምትካቸው....መሆኑን አስታውቀዋል። ኢህአዴግ የሚስማማውን ህግና ደንብ ካወጣ የማይስማማውን ሁሉ ካስወገደ በኋላ እርስ በርሳቸው በሚባሉ ተቀዋሚዎቹ የቁም ሬሳ ላይ የሚቀጥለውን ምርጫ በአሸናፊነት ለመወጣት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጠው የተቻለውን ዝግጅት እያደረገ ነው። ከወዲሁ በታየው ድልና መረጋጋት አሸናፊነቱን በሚያሳይ መንፈስ እየፏለለ ነው። ኢህአፓዎች ከሐሰተኞቹ ኢህአፓዎች በመላቀቃቸው ወይም በመወጋገዳቸው የየፊናቸውን ሁለት እውነት ይዘው ቀጣዩን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት እየገሠገሡ ነው። የገዛ ሤራቸውን ጭምር ትንቢት ያስመሰሉት አቶ ልደቱ፣ መሬት ወድቆ ያገኙትን የቅንጅት ጣት "ባትጋሩኝ!" ብለው ህጋዊ አስደረገው ለብቻቸው በመያዛቸው የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ ቃል ያጠራቸው ይመስላል። ስድስት ዓመት ታስረው የወጡት የቀድሞ የህወሓት መስራች እንዲሁም ወታደራዊ ቁንጮና ባለሥልጣን የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ "ሁሉንም ነገር ለይቼ አይቸዋለሁ" በሚል የድል መንፈስ ተሞልተው መፍትሔው ፍንትው ብሎ የታያቸው መሆኑን እየነገሩን ነው። ማሰር መታሰርን ያዩትና "ካሁን በኋላ ትግሌ ለመሞከር ሳይሆን ውጤት ለማምጣት ነው" የሚሉት አቶ ስዬ፣ እያሳዩ ያሉት በራስ መተማመን ለሳቸው ብቻ የተገለጸ ልዩ ሚስጥር ያለ አስመሏቸዋል። በመንግሥትነት የተቀመጠውም ፓርቲ ይሁን በያቅጣጫው ለኢትዮጵያ የሚበጃትን መፍትሄ በሞኖፖል መያዛቸውን የሚያምኑ ፖለቲከኞች በየራሳቸው አንጻር ባስመዘገቡት ድል እየረኩ በየራሳቸው ዓለም ጠፍተዋል።

ህዝቡ ግን ምን ያስብ ይሆን? ህዝቡ ምን እንደሚያስብ ለማወቅ እኛ አንችልም። ለመገመትም ሥልጣኑም እውቀቱም ውክልናውም የለንም። ግን ቢያንስ ቢያንስ የየራሳችንን ሀሳብ የመግለጽ መብት አለንና ስለህዝቡ ሆነን ባንናገርም ስለራሳችን መናገር እንችላለን። እኛ አንድም እንሁን ሁለት ሰዎች፣ በሆነው ነገር አዝነናል። ማን እንዳሸነፈን ባናውቅም የሽንፈት ስሜት አድሮብናል። ሀዘን ገብቶናል። በየፊናው የምንሰማው ቅጥፈት ያስዝነናል። ሽማግሌው፣ ወጣቱ፣ መሪው፣ ጀሌው፣ ባለሥልጣኑ፣ ሎሌው፣ ድብን አድርገው በአሸናፊነት ሲዋሹ እያየን ነው። ልክ ልካቸውን ነግረን አፋቸውን ማስያዝ አለመቻላችን ይሰማናልና አቅመቢስ መሆናችን ያስዝነናል። አጅሬ ሁሉ ሊቅ ሆኖ ኢትዮጵያን ለሚያህል አገር "መፍትሄው እኔ ነኝ" ሲለን ከጅል ልቡ ተንጠራርቶ የወጣውን ድፍረት ስናይ - አበስገበርኩ ይህን ያህል ሞተናል እንዴ- ያሰኘናል። ምንም ነገር ማድረግ አለመቻል ምንኛ መታፈን ነው። በሰከንድ ውስጥ 6ሺ ጊዜ የሚርገበገብ ምላስ ያለው ሁሉ በተንጣጣ ቁጥር፣ ለአገሩ የፈጠነ ሲመስለው እናያለን። ዝግ ብሎ በእርጋታ የሚያወራው አዛውንት፣ እንዲያ በማድረጉ ብቻ፣ ከእርጋታው ረግቶ የሚያረጋጋ ሀሳብ የሚፈልቅ መስሎት በውሽት ሲሟዘዝ ስናይ ዕድሜን ብቻ የማክበር ባህላችን ምን ያህል አፍኖ እየገደለን እንደሆነ እነገነዘባለን።

አንዳንዴ ደግሞ አጓጉል መንጋም ያስፈራናል። ለመጣው ለሄዴው ሁሉ የሚያጨብጭብ ለጠላው ለወደደው ሁሉ እኩል የሚንጋጋ መንጋ ያስፈራናል። አባራሪና ተባባሪን መለየት አቅቶት፣ ወደዚያና ወደዚህ ሲነዳ ማየቱ ጨጓራ የሚልጥ ትዝብት ይሆንብናል። ባለፈው የሰጠናችሁን ገንዘብ የት አደረሳችሁት እያለ እዚያው በሌብነት እየከሰሳቸው እዚያው ደግሞ ገንዘብ አውጥቶ ሲያሸክማቸው ስናይ ከገንዘቡም ከእምነቱም አለመሆኑን የማያስተውል ይህ መንጋ ምንኛ ከንቱ ነው ያሰኘናል። ራሱ መርጦ ራሱ ላይ ያነገሠው አልባሌ ዘውድ፣ ሊያወርደው የማይችለው ሸክም ሆኖበት፣ ሲጫነው ማየቱ፣ ምንኛ አቅመ ቢስ መንጋ ነው አሰኝቶ ያሳዝነናል። የመንጋው ስድብ፣ ትዝብቱ፣ ንቀቱ፣ እርግማኑና ውግዘቱ ሁሉ ምንም ሳያደርጋቸው በፈለጉ ጊዜ መልሰው ጠርተው የሚያስጨበጭቡት መንጋ ሆኖ መገመቱ ምንኛ ያንገበግባል። የተሰማማ ድምጽ መፍጠር አቅቶት ጥቅምና ጉዳቱን መለየት ተስኖት በአጠቃላይ ጥቅሞቹ ላይ እንኳ አንድነት አጥቶ ማንም አርባ ቦታ የሚከትፈው መንጋ የሞላባት አገር ተስፋዋ ምን እንደሚሆን መገመት አስቸጋሪ ቢሆንም ኃይለኞች ሳይሆኑ ደካሞች እንኳ ሊነግሡ የሚችሉባት አገር መሆንዋ ግልጽ ይመስላል። ይህ የባቢሎን መንጋ፣ ይህን ያህል እንኳ አልሞትኩም የሚለው ትእቢቱን ትቶ፣ የሚመሩትን፣ የሚያስተባብሩትን፣ የሚያጋፍሩትን፣ የሚከፍሉ የሚያጣብቁትን መድረክ አጣባቢ ምናምንቴዎችን ከደህናዎቹ ለይቶ፣ ጌቶቹን ሳይሆን አገልጋዮቹን የሚሾም የሚሽርበት ኃይል ካላበጀ፣ ነገሩ ሁሉ አሁን ባለው መልኩ ይቀጥላል። "ዝምብሎ ብቻ ምን ዋጋ አለው?" ማለት አያስፈልግም። ማንም ለማንም ዋጋ አይሰጥም። ዋጋን ማግኘትስ ከራስ ነው። ለራስህ ዋጋ ስጥ! አገልጋይ መሪን መፍጠር ካልተቻለ ጥሩ ሎሌና ተከታይም መሆን ይቻላል። እንዲህ ነኝና የጠቅል አሽከር ማለትም ወግ ነው። ለነገሩ ተከታይም ሎሌም ዋጋ አለው። ጥሩ ሎሌ ግን የሚበጀውን ጌታ ከማይበጀው ጌታ ለይቶ ያውቃል። ጥሩ ሎሌ ሞራል ያውቃልና የጌታውን ድክመት እንኳ እያሟላ በፍቅርና ታማኝነት ይሰነብታል። አገር መገንባት በመሪዎች ብቻ አይመጣምና እንዲህ ያለ ሎሌነት የገባው መንጋም ያስፈልጋል። መመራትም አገር ይመራል። ጥሩ ተከታይነትም መሪን ይፈጥራል። አመራር ከመሪዎች ብቻ አይገኝምና አጓጉል መንጋዎችም ኃላፊነቱን እንውሰድ። (ዘኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)