Wednesday, February 4, 2009

ሰላም ወዳድ ረሀብተኞች!

ከረሀቡ ይልቅ ስለረሀቡ የሚወራው ሰልችቶናል - ምክንያቱም በዓይናችን ሙሉ ማንንም ቀና ብለን እንዳያይ ያደርገናል። ለአንዳንዶቻችን የረሀብ ጉዳቱ እሱ ብቻ ነው። ምክንያቱም እኛንም ከተራቡት ይደምረናል። እውነት ለመናገር አንዳንዴ እግዜር ይቅር ይበለን እንጂ የፈለገው ህዝብ እዚያ ፍግም ብሎ ወሬው እፍንፍን ተደርጎ ቢቀር የምንመኝ አንጠፋም። ሸሽተነውና አምልጠነው የመጣነው ህዝብ ጠግበን የምናድርበት አገር ድረስ ተከትሎ መጥቶ ለምን ይረብሸናል? እኛንም እንደ ረሀብተኛ ከሱጋር ደምሮ ሲያዋርደን ያናድዳል። ይኼ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ነገር እንዴት ያለ ፈተና ነው? አንዳንዴማ እንደው አገላለጹ ጠፍቶ ነው እንጂ አብረውን ለሚሰሩትና በ ሲ.ኤን.ኤን ለሚያዩት በጋዜጣና ኢንተርኔት ለሚያነቡት ፈረንጆች ሁኔታውን ብናስረዳቸው ደስ ይለናል። አለ አይደል- ይኸውላችሁ እውነት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ አለ ግን ብዙ ቦታ አይደለም። አሁን ለምሳሌ የኛ ቤተሰቦች ደህና ናቸው። አዲስ አበባ ብትሄዱ ረሀብ በአገሪቱ ያለ አይመስላችሁም። ከፈለጋችሁ ፎቶግራፍ እናሳያችሁ… የተራቡትኮ …

በአስተሳሰብ እንጂ በቁጥር “ትንሽ” ለማንባል ሰዎች በረሃብ ከሚሞተውና ከሚቸገረው ሰው ይልቅ ረሀቡ የሚነገርበት ሚዲያ ያናድደናል። ስማችንን እንወደዋለን። ለምን አይተውንም ማለትም ይቃጣናል።

ግን አልተዉንም። ወሬው እንደገና መጣ። ዓለምም ሰምቶት እንደማያውቅ ዜናውን ይቀባበለው ጀምሯል። ኢትዮጵያውያንም ዓለም ለምንድነው በረሀብ ብቻ የሚያውቀን ፣ ታሪክ አለን፣ አክሱም ላሊበላን እዩልን፣ በሩጫም እንታወቃለን አሁን ቤጂንግ ላይ የሆነውን ተመልከቱልን። እስክስታና ዳንኪራችንን እዩልን፣ ዶሮ ክትፎና ቀይወጣችንን ቅመስሉን። በሀበሻ ልብሳችን እንዳጌጥን በራሳችን ፊደል እንደጻፍን በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያናችን እየኮራን ባህላችንን እያስተዋወቅን ነው። ኢትዮጵያን በረሀብ ብቻ አትወቋት ይህንም ይህንንም እነዚህንም አላት እያልን ነው። ግን የትኛውም ገጽታችን ፊቱ ያገጠጠ፣ ሆዱ ያበጠ፣ አጥንቱ ያፈጠጠ ረሀብተኛ ህጻንን ገጽታ አይሸፍነውም። እሱ በልጦና ፈጥኖ ይታያል። ይሄ የሐረር ልጅ፣ የጎንደር የትግራይ ልጅ፣ ይሄ አማራ ይሄ ኦሮሞ እያልን የምንመጻደቅበት፣ ይሄ አመድ በዱቄት የሚስቅበት፣ ይሄ አገር ተገልቦ የምንከናነብበት የድንቁርና ኩራት፣ በአደባባይ የጎደፈው ስማችንን አያነጻውም።

የዓለም ኢኮኖሚ ከመዛባቱ በፊት ረሀብ ነበር። ነዳጅ ከመወደዱ በፊት ረሀብ ነበር። በጥጋብም ጊዜ ረሀብ ነበር። አለም ጠግቦም ተርቦም እኛ ሁሌ ያው ነን። እድገት ብቻ ሳይሆን ያውም “ፈጣን እድገት” በተመዘገበበት ባሁኑ ወቅትም ረሀብ አለ። ግን ለምንድነው ይሄ የሚሆነው? መልሳችን “በቃ እንዴት ብዬ ላስረዳህ…” አይነት ነገር ነው። ግን ራሳችንን ነጻ አውጥቶ ሌላውን የሚያስወቅስ ባህል ስላለን የረሃብ ምክንያቱ ሁሌም ሌላው አካል ነው። ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ምክንያት ለመደርደር ጣት ለመቀሰር የሚሻማ ትውልድ የሞላባት አገር መስላለች። ምክንያቱ ተመሳሳይ ይሁን አይሁን እሱ ሌላ ነገር ነው። መልሱን በሰከንድ ውስጥ ለመግለጽ የማይደፍር ኢትዮጵያዊ ግን ታይቶ አይታወቅም። እኔ እንጃ እኔ ምንም ሊገባኝ አልቻለም ወይም ይቅርታ አድርግልኛልና በደንብ አስቤበት አላውቅም… የሚል ትሁት ኢትዮጵያዊ ማግኝትማ የማይታሰብ ነው። እንኳን ይቺን የዝምብ ጠንጋራ የሚያውቅ ህዝብ ነው። ከህዝብ የሚሰወር ነገር የለም። ህዝብ ሁሉን ያውቃል የሚባል እውነት አይሉት ተረት አለ። እንዲህ የሚያደርገን ድንቁርና ነው የሚባል ክስና ማንኳሰስም አለ። በአንድ ራስ አስር ምላስ እንዲሉ ያልተሰጠ ምክንያት የለም።

ፖለቲካው ነው- መንግሥት ነው- ዓለም ባንክ ነው- ኋላ ቀር አስተራረስ ነው- የመሬት ፖሊሲው ነው- አባይ ወንዝ ነው….ያልተባለ ያልተጻፈ ያልተጠና ነገር የለም። ያልተቀረጸ ፖሊሲ ያልተቋቋመ ግብረሃይል የለም። ሠፈራና መንደር ምስረታ፣ ድህነት ቅነሳ፣ ኤክስቴንሽን፣ ፈጣን እድገት፣ ቡና፣ አበባ፣ ዘንባባ ያልተባለ ያልተጠራ ያልተፈከረ የመፈክር ዓይነት የለም። ከሁሉ ከሁሉ የዘለዓለማዊው መንግሥታችን የኢህአዴግ ስትራቴጂ ይሻላል። ቢያንስ የረሀብተኛውን ቁጥር ተከራክሮ አስቀንሷል።4ሚሊዮን ናት። በዚያ ላይ “የሚሊኒየሙ ጎል” የሚባል ድንቅ ነገር አለው። ረሀብን በዚህ ሚሊኒየም (1ሺ ዓመት ውስጥ) እናጠፋለን ብሏል። ሆዱን ከፍቶ፣ ዓይንና ጆሮውን ዘግቶ አስተዋይና ብልህ መሪ እያለ የሚያደንቃቸው የልማት መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ግን የኢትዮያን ህዝብ በቀን 3 ጊዜ እንዲበላ የማድረግ ህልማቸው ካለፈ 7 ዓመት ሆኗል። ከ10 ዓመት በኋላ ነበር ያሉት- አሁን 17 አልፏል። በሰሞኑ የፓርላማ ስብሰባቸውም ይኼ አሁን ያለው ረሀብ “ጊዜያዊ ነው” የሩቁ ግባችን ግን ብሩህ ሆኖ ይታየናል ታገሱን ብለውናል። እሳቸው ታገሱ ባይሉም መታገስ አይቀርም። ምክንያቱም “ህዝባችን ታጋሽ ሆደ ሰፊና ቻይ ህዝብ ነው” በዚያ ላይ እንኳን ለኢትዮጵያ የአፍሪካ ረሀብ እንዴት ሊወገድ እንድሚችል መጽሐፍ የጻፈ ታላቅ ሰው እየመራት ኢትዮጵያ ምን ትሆናለች ብለን እንሰጋለን። እንቸለዋለን!

ግፍን መቻል ረሀብን መቻል ስደትን መቻል መለያችን ነው። ሰላም ወዳድ ረሀብተኞች ነን። አስተዋይ ህዝብ ነን። ማስተዋላችን ግን ወደኋላ ነው። እቅዳችን ትዝታችን ነው። ዛሬን ሳይሆን ትናንትን እየኖርን ነው። የነበርንበትን ሳይሆን ያልነበርንበትን እየናፈቅን ነው። ተስፋችን ታሪካችን ነው። መሪያችን አሁንም እነ ኣጼ ቴዎድሮስ ናቸው። ግን እሱንም በወጉ አልያዝነውም። የዛሬው ቅንጅታችን ቴዎድሮስን ሲያስጨንቅ እንደነበረው “ዘመነ መሳፍንት”- ዘመነ ቅንጅት ሆኖ ያስጨንቀናል። ኃይሉ ለብቻው ብረሃኑ ለብቻው ብርቱካን ለብቻዋ… እያልን ቅንጅቶች አንድም- አንድ ሺም ሲሆኑብን እንችላቸዋለን! እኔን ብትንካ የኔ ሕዝብ አይለቅህም የሚለንን የወያኔ ሓርነት ትግራይን የጎሳ ፖለቲካ ሸፍጥ መሆኑን ብናውቅም እውነት ቢሆንስ የሚለው ጥርጣሬ ያስጨንቀናልና እንችለዋለን። እናንተም ደግሞ ይህን መንግሥት አምናችሁ እሱንና እኛን አንድ ላይ ደምራችሁ እንዳትመለከቱ እንማልዳለን የሚሉን የዋሆዎችና ቀጣፊዎች የተደባለቁበት ጩኸትም ያስጨንቀናልና እሱንም እንችለዋለን። ስለ ትግራይ ህዝብ ስንል ወያኔ እንችለዋለን። ስለ ኦሮሞ ህዝብ ብለን ኦነግን እንታገሰዋለን። ስለ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን ብለን፣ ስንበስልለት ሊበላን ለሚቀቅለን ሻእቢያ ቻይነቱን ሰጥቶናል።

መድሃኒታችን ራሱ በሽታ ስለሚሆንብን ፍርሃታችንን እንችለዋለን። በሽታ ሁሉ ግን ስለቻሉት አይድንም! ቻይነት መድኃኒት አይደለም። ትእግስት ሁሉ ፈውስ አይደለም። ለሁሉም ጊዜ አለው ማለት ለጊዜ ባለቤት የለውም ማለት አይደለም። አቶ መለስ ጃጅተው አርጅተው ያልፋሉ። ወያኔ የሚባል ድርጅት ሄዶ ሄዶ ፈንድቶ ይፈራርሳል። ይህ በራሱ ሂደት ይሆናል። ይህ ሁሉ ግን ማታ ተኝተን ጧት የሚጠብቀን አዲስ ክስተት አይደለም። እኛንም አብሮ ያስረጃል። እኛንም አብሮ ያፈራርሳል። በዚህ አግባብ ለሁሉም ጊዜ አለው ማለት ይህ የኛ ጊዜ አይደለም የሚል ተሸናፊነትን የሚወልድ ተው ቻለው ሆዴ ነው!

እኔነታችን በራሳችን ተሸንፏል። ዜግነታችን በምክንያታችን ጠፍቷል። ምክንያት! ምክንያት! ምክንያት! ሰበብ- ማሳበብ -ማላካክ-መወንጀል -ሌላው ነው- ሌላው ነው- ሌላው ነው! እኛ የለንበትም!

እውነት ነው ከሌለንበት የለንበትም! ባላጠፋነው አንጠየቅበትም። ግን ኢትዮጵያና ረሀብ ተያይዘው በቴሌቪዥን ሲመጡ ስሜታችን መነካቱ አይቀርም። እንደማንኛውም የዓለም ዜጋ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ይሰማናል። ስሜታችን ለአፍታም ቢሆን ይጠይቀናል። ከተሰካልንም ያመናል። በጣም ከተሰካልንም በዚህ ውስጥ ምንም ማድረግ የማንችል ትንኝ መሆናችን ይሰማናል። ከሁሉ ከሁሉ ግን እኛ እንደተሰማን ምንም የማይሰማቸው ወይም ዜናውን እንደ ኦሎምፒክ ወሬ ወይም እንደ ሱናሚና ካትሪና አውርተውና ትንሽ አስተያየት ጣል አድርገው የሚያልፉ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ስናስብ እንቀናለን። እንደነሱ እውቀት ገብቶን ሶ ዋት ድሮስ ምን ይጠበቃል፣ አለማለታችን ከተራበው ብቻ ሳይሆን ከጠገበውም ኢትዮጵያዊ አለመሆናችንን ያሳያልና ይሰማናል።

ወጣም ወረደም ግን ራሳችንን ከህሊናችን ነጻ ማውጣት እንፈልጋለን። ምክንያቱም ስደት ከአገር ብቻ ሳይሆን ከህሊናም ጭምር ነውና ጨቅጫቃ ህሊና አያስፈልገንም። የተራቡት ነገ በረሃብ ይሞታሉ። የጠገብነው ግን አስቀድመን ሞተናልና ምንም መጨነቅ አይገባንም። ምክንያቱም ሰላም እንፈልጋለን።ይህም ስለሆነ ነው ዓይናችንን እንጂ ልባችንን አያመውም። ጆሯችንን እንጂ ህሊናችንን አይሰማውም። በዚያ ላይ ደግሞ እድለኞች ነን፤ እድሜ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶቻችንና ለመንግሥታችን የዚህ ሁሉ ምክንያት እነሱ ናቸው። እነሱ ባይኖሩ ይህ ሁሉ አይሆንም ነበር። አይደል? (ዘኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment

Zethiopia Event

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ እና ባለ ታሪኮች

ከዘኢትዮጵያ ታሪክ  እና ባለ ታሪኮች
ይህን ቅርስ በአደራ ጠብቀውና ተከላክለው ያቆዩት ብ/ር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ ነበሩ። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት ቤተመንግሥትን በዋናነት ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ጄነራል ፍሬሰንበት ህይወት ጋር አብሮ የሚጻፍ ብዙ ታሪክ አለ። ለምሳሌ እነዚህ ይገኙበታል (ለማንበብ ፎቶ ግራፉን ይጫኑ)